ዛሬ በበርካታ የጥበብ ሥራዎቹ የብዙዎችን ልብ ያሸነፈውና የመድረክ አድማቁ አርቲስት ሽመልስ በቀለ የ60 ዓመት የሕይወት ማዕበልን አልፎ አልማዛዊ የልደት በዓሉን የሚያከብርበት ልዩ ቀን ነው!
አርቲስት ሽመልስ በቀለ ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ከተማ በፍልውኃ አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በልዑል አልጋ ወራሽ አሥፋ ወሰን የሕፃናት ማደሪያና በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በዳግማዊ ምኒልክና በኮልፌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከታትሏል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ፋክልቲ (4 ኪሎ) የኢንጅነሪንግ ትምህርቱን ቢጀምርም፣ ለሕብረተሰብ ሳይንስና ለኪነ-ጥበብ ያለው ጥልቅ ፍቅርና ዝንባሌ አቅጣጫውን ሙሉ በሙሉ ወደ ሚዲያውና መዝናኛው ዘርፍ እንዲያዞር አድርጎታል።
በመዝናኛውና በኮሙኒኬሽን ዘርፍ "Infotainment Host" በመባል የሚታወቀው አርቲስት ሽመልስ በቀለ፣ በትያትር፣ በማስታወቂያ፣ በሚዲያ ዝግጅቶችና በመድረክ መሪነቱ (MC) የጎላ ስምና ገናና አሻራ አለው። ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 32 ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ዝግጅቶችንና ማስታወቂያዎችን በማቅረብ የኢንዱስትሪው ግንባር ቀደም ምሰሶ መሆን ችሏል።
አባቱ አቶ በቀለ ሽመልስ ለ38 ዓመታት በቅዱስ ዮሴፍና በካቴድራል ትምህርት ቤቶች በርካታ ታዋቂ የሀገራችንን ባለሙያዎች ያፈሩ የተከበሩ መምህር ነበሩ። አርቲስት ሽመልስም የዚያ ታላቅ አባት ልጅ በመሆን መልካም ሥነ-ምግባርንና አገልግሎትን ወርሶ ለዚህ ደረጃ የበቃ ታላቅ ሰው ነው።
ዛሬ 60ኛ ዓመት የልደት በዓሉን በሚያከብርበት በዚህ መልካም ቀን፣ ፈጣሪ ሙሉ ጤናን፣ ረጅም ዕድሜንና ተጨማሪ ስኬቶችን እንዲታደለው እንመኛለን!
ጉርሻ page
🌴🌴🌴









